ከጢልቴ ዱሜ ግርጌ
በእንዳለ ደበላ ሀዋሳ ኢዜአ “ተረግዞ ለመወለድ ያለ ተጨማሪ ቀናት ዘጠኝ ድፍን ወራት ብቻ የፈጀበት በርካቶችን ያስደመመ ልጅ በሀዋሳ ተወልዷል” አሉኝ አንድ በእድሜ የገፉ አዛውንት፡፡ እንዴ ታዲያ እርግዝና እኮ ዘጠኝ ወር ነው የሚፈጀው በዘጠኝ ወር መወለድ ያስደመመበት ምክንያት አልገባኝም አልኳቸው፡፡ “አይ ልጄ አሉኝ በቅዱስ መጽሀፉ የሰፈረውን እንኳን ብናይ ማርያም እየሱስ ክርስቶስን የወለደችው ከዘጠኝ ወር ከዘጠኝ ቀናት እርግዝና በኋላ ነው” አሉኝ፡፡ “እናቶችን ብትጠይቅ ልጆቻቸውን ለመውለድ ከዘጠኝ ድፍን ወራት ተጨማሪ ቢያንስ ዘጠኝ ቀናት ይኖራል ፡፡ ይህ ልጅ ግን ዘጠኝ ድፍን ወር ብቻ የተረገዘ ነው ፡፡ ያለ ተጨማሪ ቀናት ተወለደ ”፡፡ በቅርቡ ወንድ ልጅ ያስታቀፈችኝ ውዷ ባለቤቴ ልጁን የተገላገለችው አስር ወር ከሰባት ቀን መሆኑን ትውስ አለኝና የአዛውንቱን ወግ ማድመጥ ቀጠልኩ፡፡ አቶ ታደሰ ባላ ከሀዋሳ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝ የሸበዲኖ ወረዳ ማዕከል በሆነችው ለኩ እንደተወለዱና በተለምዶ እርሻ ጣቢያ እየተባለ በሚጠራው የመንግስት እርሻ ድርጅት ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተው ጡረታ ከወጡ 12 ዓመት እንደሆናቸው አወጉኝ፡፡ “ዛሬ በዘጠኝ ወሩ የተወለደውን ልጅ ለማየት መጣሁ እናም በእድሜዬ እንደዛሬው ተደምሜ አላውቅም” ባይ ናቸው ፡፡ “እንዲህ ፈጥኖ ይሆናል ብዬ በፍጹም አልጠበቅሁም ነበር ፡፡ ግን ሆኖ ሳየው አስደመመኝ ፡፡ በዚች ከተማ ባልወለድባትም የስራን ሀሁ የጀመርኩባት ናት”፡፡ “ከ40 አመት በላይ የኖርኩባት በመሆኑ በዚህ መልክ በአጭር ጊዜ የሆነ ታምር ገጥሞኝ አያውቅም” ብለው ከታሪክ ያወቁትን የሀዋሳን አመሰራረት አጫወቱኝ፡፡ እሳቸው ያወጉኝን በከተማዋ ታሪክ ዙሪያ በዘለቀ ከበደና ሰርካለም አለማየ