ለዝናብ እጥረት ተጐጂዎች የ230 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ተጠየቀ
- 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ ይፈልጋል የኢትዮጵያ መንግሥትና ለጋሾች በጋራ በመሆን ባወጡት የሰብዓዊ ድጋፍ ሰነድ፣ በክረምት ዝናብ እጥረት ምክንያት 230 ሚሊዮን ዶላር ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ይፋ አደረጉ፡፡ ነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮችና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ፣ እ.ኤ.አ. በማርች 2015 ወጥቶ የነበረውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰነድ በመከለስ፣ ቀደም ሲል ተገምቶ ከነበረው በተጨማሪ 1.6 ሚሊዮን ሕዝብ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱም በበልግና በክረምት ወቅቶች በኢትዮጵያ የታየው የዝናብ እጥረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ሰብዓዊ ዕርዳታ ያስፈልገዋል ተብሎ ተገምቶ ከነበረው 2.9 ሚሊዮን ሕዝብ በተጨማሪ 1.6 ሚሊዮን ሕዝብ የሰብዓዊ ዕርዳታ በመሻቱ፣ አጠቃላይ የተረጂዎች ቁጥርን 4.5 ሚሊዮን እንዳደረሰው የመንግሥትና የሰብዓዊ ድርጅቶቹ የጋራ መግለጫ ያስረዳል፡፡ ለአፋጣኝ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጐቶች የኢትዮጵያ መንግሥት 700 ሚሊዮን ብር ወይም 33 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን መግለጫው ያስረዳል፡፡ ‹‹የአውሮፓውያኑ 2015 ሲጀምር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ስለበልግ የአየር ሁኔታ ከተነበየው እጅግ የከፋ የዝናብ እጥረት በመከሰቱ፣ የምግብ እህልና የተመጣጠነ ምግብ እህል ችግር ተከስቷል፤›› በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ተጠባባቂ ኃላፊ ዴቪድ ዴል ኮንቴ ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ አምራች የነበሩት የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በተለይም የአርሲና የምዕራብ አርሲ አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳስፈለጋቸው መግለጫው ያብራራል፡፡ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የተከሰተው የከብቶች