የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲስተካከል እንግሊዝ ጥያቄ አቀረበች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ካለው ቀውስ ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮች እንዲስተካከሉ እንግሊዝ ጠየቀች፡፡  
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲስተካከል እንግሊዝ ጥያቄ አቀረበች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ ከእንግሊዝ አምባሳደር ሱዛና ሞርሄድና ከኤምባሲው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት
ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ እየተከሰተ ካለው ቀውስ ጋር ተያይዞ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር እንዳለ፣ ኢትዮጵያም ይህን ችግር እንድታስተካክል እንግሊዝ ምክረ ሐሳብ ማቅረቧ ታውቋል፡፡
ይህ ምክረ ሐሳብ የቀረበው ኢትዮጵያና እንግሊዝ ለአራተኛ ጊዜ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ያተኮረ የጋራ ውይይት፣ ሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ፣ በኢትዮጵያ የስደተኛና ከስደት ተመላሽ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች፣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ሱዛና ሞርሄድና የኤምባሲው የሥራ ኃላፊዎች፣ የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዲኤፍአይዲ) ዳይሬክተሮችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተገኝተው ነበር፡፡
የውይይቱ አጀንዳዎችም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ ስደት፣ የመንግሥት ተጠያቂነትና ግልጽነት ነበሩ፡፡ የሁለቱ አገሮች የጋራ ውይይት የተካሄደው በዝግ ቢሆንም፣ የሪፖርተር ምንጮች እንደጠቆሙት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያሉ ችግሮችን የእንግሊዝ መንግሥት ተወካዮች በዝርዝር አውስተዋል፡፡
አንድ የእንግሊዝ ዲፕሎማት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ስደተኞችን በማስተናገድ ግንባር ቀደም አገር ብትሆንም በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ችግሮች አሉባት፡፡ ‹‹ይህንን ያህል የስደተኛ ቁጥር ተቀብሎ ማስተናገድ ከባድ ነው፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ይቆማል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ግን ጊዜ የማይሰጠው ነው፤›› ሲሉ ዲፕሎማቱ ጠቁመዋል፡፡
በሁለቱ አገሮች ውይይት ላይ ከአራት ዓመታት በፊት የመን ተይዘው ለኢትዮጵያ ተላልፈው የተሰጡት የትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ተነስቶ ውይይት መደረጉን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በውይይቱ ላይም አቶ አንዳርጋቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የእንግሊዝ መንግሥት ማብራሪያ መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በተሰጠው ምላሽም እንደ ማንኛውም እስረኛ በእስር ላይ እንደሚገኙና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደማይካሄድባቸው መገለጹ ታውቋል፡፡
ሁለቱ አገሮች ከአፍሪካ በተለይም ከምሥራቅ አፍሪካ እየፈለሱ ወደ አውሮፓ ስለሚሄዱ ስደተኞችና ስለሚደርስባቸው ጉዳት ውይይት መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ስደትን ማስቆም እንዳለባት የእንግሊዝ መንግሥት መግለጹ ታውቋል፡፡ እንግሊዝ ሕገወጥ ስደትን ለማስቆምና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ያግዝ ዘንድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ቃል መግባቷ ተሰምቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ሒሩት እንግሊዝ የኢትዮጵያ ትልቋ የልማት አጋር መሆኗን ተናግረዋል፡፡ እንግሊዝ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች መሆኗን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በተለያዩ መስኮች በሚደረጉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ገና በማደግ ላይ ያለች አገር በመሆኗም ችግሮች እንዳሉና በአሁኑ ወቅት ብዙ መሻሻሎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር