የሲዳማ ቡና ኣብቃዮች እና ያልከፈሉት በቢሊዮኖች የምቆጠር ውዝፍ እዳ

የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ያጋጠማቸውን ኪሳራ በማስመልከት ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በፋይናንስ ኢንዲስትሪው ውስጥ እንግዳ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሰኔ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው መመርያ፣ በባንክ ዘርፉ ውስጥ ያለተለመደ ስለነበር ጉዳዩ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡
ገዥው ባንክ የአገሪቱ ባንኮች እንዲተገብሩት ያስተላለፈው ሰርኩላር፣ ከተለያዩ ባንኮች ብድር የወሰዱ የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች የነበረባቸውን የብድር ዕዳ ከሌሎች ተበዳሪዎች በተለየ እንዲታይና ለብድር አከፋፈል ከተቀመጠው መመርያ ውጭ እንዲስተናገድ የሚያዝ ነው፡፡
የአገሪቱ ባንኮች የሚሰጡትን ብድር እንዲሁም የአመላለስ ሥርዓቱን የተመለከተው ይህ የገዥው ባንክ መመርያ፣ ለአንድ ብድር የተሰጠው የመክፈያ ጊዜ ከሦስት ጊዜ በላይ ማራዘም ወይም ማስታመም እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡ የደቡብ ቡና አቅራቢዎች ግን ይህ መመርያ ሳይተገበርባቸው እንዲስተናገዱ ብሔራዊ ባንክ  ለንግድ ባንኮች የላከው ሰርኩላር ያሳስባል፡፡   
ቡና አቅራቢዎቹ ከዚህ መመርያ ውጭ ብድራቸው ከሦስት ጊዜ በላይ እንዲራዘምላቸው ከመፍቀዱም ባሻገር የነበረባቸውን ውዝፍ ብድር በወቅቱ ባለመክፈላቸው ለማስያዣነት ያቀረቧቸው ንብረቶችም እንዳይሸጡ የሚከላከል ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ለአጭርና ለመካከለኛ ጊዜ ተበዳሪዎች የብድር ማስታመሚያ ጊዜ እንደተሰጠ የሚገልጸው አንቀጽ፣ ቡና አቅራቢዎቹ ላይ እስከ መጪው 2010 ዓ.ም. ድረስ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚያዝ የሁለት ዓመት የዕፎይታ ጊዜ ሰጥቷል፡፡
በዚህ ሰርኩላር ምክንያት ባንኮች ለሰጡት ብድር መያዣ የነበሩ ንብረቶችን በሐራጅ ለመሸጥ ሲያነጋግሩ የነበሩትን የሐራጅ ማስታወቂያ አቁመዋል፡፡ ለቡና አቅራቢዎቹ የተሰጠው ይህ ዕድል፣ ከ200 በላይ የደቡብ ቡና አቅራቢዎች ያልከፈሉት ውዝፍ የብድር ዕዳ ቢኖርባቸውም ተጨማሪ ብድር እንዲያገኙ ጭምር የሚፈቅድላቸው ሆኗል፡፡
ብድር መክፈል ላልቻሉ አቅራቢዎች ተጨማሪ ብድር እንዲሰጡ የሚያዘው የገዥው ባንክ መመርያ በተለይ የግል ባንኮችን ሲያስጨንቅ ቆይቷል፡፡ አቅራቢዎቹ የተበደሩትን ብድር መመለስ ከሚጠበቅባቸው ጊዜ በላይ ያዘገዩ በመሆኑ ምን እናድርግ? የሚለው ጥያቄ ለባንኮቹ አሳሳቢ ነበር፡፡
ብሔራዊ ባንክ ከተለመደው አሠራር ውጭ በመሥራት ይህንን ዕርምጃ የወሰደው፣ የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ለተከታታይ ዓመታት በቡና ዋጋ መውደቅ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እንደረሰባቸው በማስታወቃቸው ነው፡፡ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ለባንክ ማስያዣነት በመዋላቸው፣ ንብረታቸው ከተሸጠም ሊደርስባቸው ይችላል ተብሎ የተፈራው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ ገብቶ እንደሆነም የብሔራዊ ባንክ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
የቡና አቅራቢዎቹ መንግሥት እንዲታደጋቸውና ችግራቸው እንዲቀርፍላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረቡት በደቡብ ክልል ቡና አጣቢዎችና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር በኩል ነበር፡፡ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እንደሚሉት፣ በደቡብ ክልል በተለይ በሲዳማ አካባቢ የተፈጠረው ችግር ያለመንግሥት ጣልቃ ገብነት የማይፈታ ነበር፡፡ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ለዓመታት ሲገላበጥ የመጣውን ብድር የመክፈል ጫና እሱንም ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው ቀውስ በዝርዝር ታይቶ ስለታመነበት፣ የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑንም አቶ ዘሪሁን ያስረዳሉ፡፡ ማኅበሩን ጨምሮ የደቡብ ክልል መንግሥት በጉዳዩ ላይ እጁን በማስገባት ቡና አቅራቢዎቹ በመንግሥት እንዲታገዙ በማለት ያቀረበው አቤቱታ በፌደራል መንግሥት ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል፡፡
ስለተከሰተው ችግር በቀረበው መረጃ መሠረት፣ በሐዋሳ ከተማ ብቻ ቡና አቅራቢዎቹ ከ2,400 በላይ መኖሪያ ቤቶችን ማስያዛቸው አንዱ ማሳያ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ አቶ ዘሪሁን እንደሚገልጹት፣ ይህ ሁሉ ንብረት ለዕዳ ማስመለሻነት በባንኮች ቢሸጥ ኑሮ ቀውሱ በቡና አቅራቢዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ንብረቱ በአብዛኛው የቡና አቅራቢዎቹ ቤተሰቦችና የወዳጆቻቸው በመሆኑ ችግሩ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል፡፡
ይህ ከታየ በኋላ ብሔራዊ ባንክ የተበዳሪዎቹ የዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም፣ ተጨማሪ ብድር ከፈለጉም እንዲሰጣቸው በማለት ውሳኔውን ለአበዳሪ ባንኮች ማስተላለፉ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡
ከዚህ ውሳኔ ባሻገር ቡና አቅራቢዎቹ በግል ባንኮች የሚፈለግባቸውን ብድር ጠቅልለው ወደ መንግሥት ባንክ እንዲያዘዋውሩም ዕድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ በግል ባንኮች እጅ ይገኝ የነበረውን ብድር ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲዛወር የሚደረገውም በፈቃደኝነት ቢሆንም፣ ከ200 ውስጥ አብዛኞቹ ብድራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዛውረዋል፡፡ ‹‹አሁን ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ መንግሥት ብድራችን እንዲራዘም፣ ተጨማሪ ብድር እንድናገኝና በግል ባንኮች ያለው ብድራችን ወደ መንግሥት ባንክ እንድናዛውር በማድረጉ ከሞት አድኖናል፤›› በማለት አቶ ዘሪሁን የመንግሥትን ዕርምጃ አሞካሽተዋል፡፡
የቡና አቅራቢዎቹን ብድር ከግል ባንኮች የተረከበው ንግድ ባንክ፣ የብድር መክፈያ የዕፎይታ ጊዜ በመስጠት ቡና አቅራቢዎች ተረጋግተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻሉን አቶ ዘሪሁን ጠቅሰዋል፡፡ በዕዳና በኪሳራ ችግር ውስጥ የቆየው የአካባቢው ቡና አቅራቢ ተጨማሪ ዕድል እንዳገኘ የሚገልጹት አቶ ዘሪሁን፣ በምርት ዘመኑ ለቡና ግዥ የሚያውሉት ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሥራ ማስኬጃ ብድርም እንደተለቀቀላቸው ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ሥራ ማስኬጃ ገንዘብ በኪሳራ ከገበያ ወጥቶ የነበረው ቡና አቅራቢ በሐራጅ ሊሸጥበት የነበረውን ንብረት ከማዳኑ በላይ ቡና ገዝቶ እንዲያዘጋጅ ዕድል ሰጥቶታል፡፡
ለሥራ ማስኬጃ በተገኘው ብድር አማካይነት ሥራ ፈተው የቦዘኑ መፈልፈያ ማሽኖች በአሁኑ ወቅት ዳግመኛ ወደ ሥራ መግባታቸውንና በማኅበሩ ሥር የሚገኙ ቡና አቅራቢዎችም ቡና እየገዙ በመፈልፈል ሥራ እንደተጠመዱ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በሲዳማ ዞን ብቻ ከ60 ሺሕ ቶን በላይ ቡና መሰብሰቡን፣ ይህም በአንድ የምርት ዘመን ከሚሰበሰበው ይልቅ ከፍተኛ የሚባል መጠን ነው፡፡ በዓመት ሲበሰብ የቆየው ከ35 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ቶን የሚገመት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን፣ ዘንድሮ ምርቱም ጥሩ ስለነበርና ከገበያ የወጡ አቅራቢዎችም ዳግመኛ ወደ ሥራ በመመለሳቸው ከታሰበው በላይ ቡና ሊሰበሰብ እንደቻለ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ቡና በሚሰበሰብበት ወቅት የሚወጣው የተጋነነ ዋጋ፣ የግብይት ሥርዓቱን ያስተጓጉል እንደነበር ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜ ግን እንዲረጋጋ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ለውጤቱ አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል፡፡ ለሚዘጋጀው ቡና የሚቀርበው ዋጋ አሁንም እንደሚያሳስብ ይሁንና ግን ሌሎች አሳሳቢ ችግሮች በመቀረፋቸው አቅራቢዎች እፎይታ ማግኘታቸውን የሚገልጹት የማኅበሩ ሊቀመንበር፣ በምርት ዘመኑ ከሚያገኙት ገቢ የባንክ ዕዳቸውን መክፈል እንዲጀምሩ ያስችላል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ እንዲህ ያለ የመንግሥት ውሳኔ ባይተላለፍ ኑሮ ይፈጠር የነበረው ቀውስ ቀላል እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ዘሪሁን፣ አቅራቢዎቹ ያለባቸውን ብድር ለመክፈል የሚያስችል የዕፎይታ ጊዜ ማግኘታቸውም ተጨማሪ ዕድል እንደሆነላቸው ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተረከበው የአቃራቢዎቹ ዕዳ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ እንዲከፈለው የተመቻቸው ዕድል ሌሎች የባንክ ተበዳሪዎች ያላገኙት በመሆኑ ይህንን ዕድል ቡና አቅራቢው በአግባቡ እንዲቀጠምበት ማኅበሩ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ በመንግሥት የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም እንዲችልም ለዚህ ተብሎ ከተቋቋመ ኮሚቴ ጋር ማኅበሩ እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡
ለደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች የተሰጠው ዕድል ግን በወቅቱ አነጋጋሪ ሆኖ መቆየቱ አይዘነጋም ነበር፡፡ ኪሳራ የገጠመው ቡና አቅራቢ በዚያ አካባቢ ያለው ብቻ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ አስነስቶ የነበረ ሲሆን፣ ባንኮች በብድር የሚሰጡት የሕዝብ ገንዘብስ በዚህ መልኩ መስተናገድ ነበረበት ወይ? የሚለውም አይዘነጋም፡፡ ይሁንና እንደ ደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ሁሉ በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ችግር ያገጠማቸው አቅራቢዎችን ለመደገፍ ተመሳሳይ ሥርዓት ተዘርግቶ ጥያቄዎቻቸውን ማስተናገድ እንደተጀመረ  ይነገራል፡፡
አቶ ዘሪሁንም በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያሉ ቡና አቅራቢዎች የእነሱን ዓይነት ዕድል እንዳገኙ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የእኛ ከሁሉ የከፋ ቢሆንም ይህ ዕድል መሰጠቱ ለሌሎችም ተርፏል፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ውሳኔ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ በተለይ ባንኮች ብድራቸውን እንዲያገኙ፣ በቢሊዮን ብሮች የሚገመቱ ንብረቶች በሐራጅ ከመሸጥ እንዲድኑ ከመደረጉ በላይ ተጨማሪ ብድር በመገኘቱም ከፍተኛ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ በር ከፍቷል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ትልቁ ችግር ግን ይህን መሰሉን ዕድል የማኅበሩ አባላት ምን ያህል ይጠቀሙበታል? ለሚለው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ማግኘቱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎም አሁንም ብድሩን መክፈል ካልቻሉስ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዘሪሁን፣ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ኮሚቴውና ማኅበሩ በጋራ እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡ እያንዳንዱ የዕድሉ ተጠቃሚ ብድሩን በአግባቡ የሚከፍልበት አሠራር የተመቻቸ ስለሆነ ብድሩን ለመክፈልና ከነበረው ቀውስ ለመውጣት ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ሊቀመንበሩ ይናገራሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር