ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚወዳደሩት የመድረክ ዕጩ ራሳቸውን ከምርጫው አገለሉ

‹‹ቅጽ አራት ከተሞላ በኋላ ራስን ማግለል አይቻልም›› ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በወላይታ ዞን በቦሎሶሶሬ 2 የምርጫ ክልል ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ለውድድር ከቀረቡት ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል፣
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)ን ወክለው ለውድድር ቀርበው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኃይሌ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡
‹‹ከምርጫው ራሴን ለማግለል ስወስን ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አልደረሰብኝም፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ በገጠሙዋቸው አንዳንድ የግል ጉዳዮችና የገንዘብ እጥረት ምክንያት ከምርጫው ራሳቸውን እንዳገለሉ ገልጸዋል፡፡ 
የመድረክ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው በበኩላቸው፣ ‹‹አባላችን ራሳቸውን ከምርጫ ያገለሉት በገጠማቸው ማስፈራርያና ማባበያ ምክንያት ነው፤›› በማለት በደረሰባቸው ጫና ከምርጫው ራሳቸውን እንዳገለሉ አመልክተዋል፡፡ 
ከዚህ ቀደም በየካቲት ወር እኚሁ ዕጩ ተወዳዳሪ ለእስር ተዳርገው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፣ ነገር ግን መድረክ ባቀረበው ተደጋጋሚ አቤቱታ ከእስር እንደተፈቱ ገልጸዋል፡፡ 
አቶ ተስፋዬ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከምርጫው ውድድር ራሳቸውን ማግለላቸውን ለፓርቲው አሳውቀው፣ ከፓርቲው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንዳቋረጡ ገልጸዋል፡፡ 
ዕጩ ተወዳዳሪው ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ለመድረክ ከማሳወቅ በዘለለ ያቀረቡት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ግለሰቡ ከዕጩነት እንጂ ከፓርቲው ራሳቸውን ማግለል አለማግለላቸው እስካሁን ድረስ እንደማይታወቅ ጠቁመዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ በበኩላቸው፣ ‹‹ግለሰቡ አሁንም ቢሆን ተወዳዳሪ ነው፡፡ በስሙ የመወዳደሪያ መልዕክቶችን እያዘጋጀና እየለጠፈ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ራሱን አገለለ የሚባል ተወዳዳሪ የለም፤›› ብለው፣ ‹‹ዕጩ ተመዝጋቢው የመወዳደር ፍላጐት ባይኖረው እንኳን ቅጽ አራት ተሞልቶ ወደ ኅትመት ከገባን በኋላ ራሱን ማግለል አይችልም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹ይህ የሕግ አግባብ መከበር አለበት፤›› ያሉት አቶ ደምሰው፣ ለምርጫ ክልሉም ሆነ ለቦርዱ በጉዳዩ ላይ የቀረበ ምንም ዓይነት ደብዳቤ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ ከገዥው ፓርቲ በመቀጠል በርካታ ዕጩዎችን ያስመዘገበው መድረክ ነው፡፡ መድረክ በአሁኑ ጊዜ አራት ፓርቲዎችን በአባልነት ታቅፈውበታል፡፡ እነዚህ አራት ፓርቲዎችም የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዓረና) እና የኢትዮጵያ ማኅበረ ዴሞክራሲያዊ-ደቡብ ኅብረት አንድነት ናቸው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር