“የ97 ምርጫ ግርግር በኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች መረጃ ላይ ክፍተት ፈጥሯል”

 የ1997 ዓ.ም የኮንዶሚኒየም ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ሂደት የተወሳሰቡ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ለተመዝጋቢዎች የመረጃ ሰነድ መጥፋትና አሁን ድረስ ለዘለቁ በርካታ ቅሬታዎች መነሻ ሆኗል ተባለ፡፡ 
በወቅቱ ምዝገባው በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለከተሞችና በሌሎች ተቋማት የተከናወነ ሲሆን ሁሉም ወገን የምዝገባ ተራ ቁጥሮችን ከ001 የጀመሩ በመሆናቸው መረጃዎቹ ወደ አንድ ማዕከል ሲሰባሰቡ የመደበላለቅ ችግር ፈጥሯል ያሉት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ፤ አንድ ግለሰብ በተለያዩ መዝጋቢ ተቋማት ሶስትና አራት ጊዜ የተመዘገበበት አጋጣሚ እንዳለም ገልፀዋል፡፡ 
የምዝገባ ማረጋገጫ የነበረውን ቢጫ ካርድ ተመሳሳይ ቁጥር እስከ 15 የሚደርሱ ግለሰቦች ይዘው ወደ ማዕከሉ እንደሚቀርቡ ያስረዱት አቶ መስፍን፤ “ሁሉም መረጃዎች በአንድ ማዕከል ተሰባስበው ከተራ ቁጥር 001 እስከ 453ሺህ ድረስ በመቀመጡ፣ እነሱ ቁጥራችን የሚሉትና ሲስተሙ የሚያውቀው የምዝገባ ቁጥር የተለያዩ ናቸው” ብለዋል፡፡ 
ለወቅቱ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ እንደ ችግር የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ የ97 ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው ግርግር መረጃን በተገቢው መንገድ ለማደራጀት አለማስቻሉ ነው ይላሉ አቶ መስፍን። በወቅቱ ከተማዋን እንዲያስተዳድር አደራ የተሰጠው የባለአደራ አስተዳደር ስራውን ተላምዶ ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ መረጃዎቹ በተገቢው መንገድ ተይዘው ነበር ለማለት አያስደፍርም ብለዋል - ሃላፊው፡፡ 
በወቅቱ የተበላሸውን ለማስተካከል በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን የጠቀሱት ሃላፊው፤ በ2005 ዓ.ም በተደረገው ምዝገባ፤ “መረጃን ጠፍቶብናል” ያሉ ቤት ፈላጊዎች በነባር የምዝገባ ስርአት ውስጥ ተካተው እንዲስተናገዱ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ 
የጋራ መኖሪያ ቤቶች መሠረተልማት ሳይሟላላቸው ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ በማለት የቤት ባለቤቶች ቅሬታ የሚያቀርቡ ሲሆን የገላን ሶስት ኮንደሚኒየም ነዋሪዎች እስካሁን ድረስ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸው፣ በሌላው የገላን ሳይት ደግሞ የግቢው መንገድ በተገቢው መንገድ ባለመስተካከሉ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ሃላፊው በበኩላቸው፤ የነዚህ ቅሬታዎች መነሻ ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የነበሩ ክፍተቶች ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የቤቶቹ ግንባታ 80 በመቶ ሲደርስ እድለኞች እንዲረከቡ ይደረግ እንደነበር የጠቆሙት ሃላፊው፤ በአሁን ወቅት ግን መቶ በመቶ ተጠናቀውና መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው እንደሚተላለፉ ገልፀዋል። በፊት ለነዋሪዎች መሠረተ ልማት ሳይሟላላቸው የተላለፉትም በአሁን ወቅት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሟላላቸው እንደሆነ ሃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ “አካባቢውን ለኑሮ የሚመች ማድረግ ግን የነዋሪው ሃላፊነት ነው” ብለዋል ሃላፊው፡፡ 
በስም አሊያም በሌላ የማጭበርበር ዘዴ በህገወጥ መንገድ የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ካሉ ህብረተሰቡ በጥቆማ ማጋለጥ እንደሚገባው ያሳሰቡት አቶ መስፍን፤ እንዲህ ያሉ ችግሮች በተደጋጋሚ  እንደሚያጋጥሙ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  
ኣዲስ ኣድማስ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር