በሐዋሳ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ለግምት የሚያዳግት ንብረት መውደሙ ተጠቆመ

‹‹ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል›› የታቦር ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች
‹‹አንድ ሕፃን ልጅ ብቻ ሕይወቱ አልፏል››  የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ
ምክንያቱ በውል ያልታወቀው የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ላይ በሐዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ታራ ቀበሌ አዲስ ከተማ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ የተነሳው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ፣ ለግምት የሚያዳግት
ንብረት መውደሙን ተጎጂዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የወደመው የንብረት ግምት በውል ባይታወቅም፣ ከ800 በላይ ሱቆች በመቃጠላቸው በርካታ ንብረት መውደሙን ግን የክልሉ ፖሊስ አረጋግጧል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎችና ጉዳት የደረሰባቸው ባለሱቆች እንደገለጹት፣ ገበያው ከተመሠረተ ሦስት ዓመታት ሆኖታል፡፡ ቀኑ ሞቅ ያለ ገበያ የሚካሄድበት ከመሆኑ አንፃር፣ ከሌሎቹ ቀናት በተለየ ሁኔታ እያንዳንዱ ሱቅ በሸቀጣ ሸቀጦች ተሞልቷል፡፡ ነጋዴዎች ሙሉ ቀን ሲገበያዩ ውለው ሒሳባቸውን የሚሠሩት በነጋታው በዕለተ እሑድ በመሆኑ፣ አብዛኞዎቹ ከሽያጭ የሰበሰቡትን ገንዘብ እንኳን ይዘው አለመሄዳቸውን ተጎጂዎቹ ገልጸዋል፡፡
አደጋው የደረሰበት ሰዓት አብዛኛዎቹ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ቆልፈው ወደ ቤታቸው የሚገቡበት በመሆኑና እሳቱ በፍጥነት ሱቆቹን በማዳረሱ፣ የተወሰነ ንብረት እንኳን ማዳን አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ ሐዋሳ ከተማ በተለይ የቱሪስቶችና የተለያዩ የአገሪቱ ዜጎች መዝናኛ ከተማ ከመሆኗ አንፃር፣ ድንገተኛ አደጋን ለመከላከል ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ በቂ የሆነ የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ባለመኖሩ ገበያው ሙሉ ለሙሉ ሊወድም መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በርካታ ሚሊዮን ብሮች የሚገመት ንብረት መውደሙን የሚናገሩት ተጎጂዎቹ፣ የነበራቸውን ሀብት በሰዓታት ልዩነት ማጣታቸው ለከፍተኛ ችግር እንደዳረጋቸው ገልጸዋል፡፡
በእሳት አደጋው ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም ብዙ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ቢገልጹም፣ የክልሉ ፖሊስ አንድ ሕፃን ልጅ ብቻ ሕይወቱ አልፏል ብሏል፡፡ ነዋሪዎች ግን የፖሊስ ቁጥር እንዳልተዋጠላቸው ይናገራሉ፡፡ 
የክልሉ መንግሥት ለጊዜው ዕርዳታ እያደረገላቸው መሆኑን የገለጹት ተጎጂዎቹ፣ ራሱ ፈቅዶላቸው በጥሩ ሁኔታ ተደራጅተውበት የነበረ ንብረታቸው መውደሙን ተመልክቶ፣ ዕርዳታው እስከ መጨረሻው እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡ የክልሉ የፖሊስ ልዩ ኃይል ፈጥኖ በመድረስ ከፍተኛ የሆነ ዕርዳታ እንዳደረገላቸው የገለጹት ተጎጂዎቹ፣ ለአደጋ መከላከያ በተለይ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር በፍጥነት ደርሶ የሚታደግ የተደራጁ የተሽከርካሪዎች ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የከተማው ነዋሪዎች ተረባርበው ባገኙት ነገር ያደረጉትን ጥረት ተጎጂዎቹ አድንቀው፣ እነሱ ባይደርሱ ኖሮ እሳቱ ወደ ሌላው የከተማው ክፍል ሊተላለፍ ይችል እንደነበር አስረድተዋል፡፡
የሐዋሳ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አደጋው እንደደረሰ ፈጥኖ በመድረስ እሳቱን የማጥፋትና ሌሎች ችግሮች እንዳይደርሱ ልዩ ጥበቃ በማድረግ፣ ከኅብረተሰቡ ጋር ባደረገው መረባረብ እሳቱን በ30 ደቂቃ ውስጥ መቆጣጠር መቻሉን ምክትል ሳጅን ዓይንአዲስ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ የተቃጠሉት የሱቆች ቁጥር ገና እየተጣራ መሆኑን ጠቁመው፣ ገበያው ሙሉ በሙሉ መውደሙንና የሱቆቹ ቁጥር እስከ 800 ሊደርስ እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ የእሳቱ መነሻ ምክንያት ገና እየተጠራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ሳጅን ዓይንአዲስ፣ አንድ ሰው እሳት ሲያቀጣጥል እንደነበር በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር ውሎ በምርመራ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የወደመውን ንብረት ግምት በተመለከተ በምርመራ ባለሙያዎች እየተጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የእሳት ቃጠሎ አደጋውን በሐዋሳ ማዘጋጃ ቤት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና ባለሙያዎች በክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል አድማ በታኝ ተሽከርካሪ፣ ከሕዝቡ ጋር በመተጋገዝ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን አክለዋል፡፡ በአደጋው የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሕፃን ሲሞት፣ አንዲት የ50 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እናት የመቃጠል አደጋ ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ የካቲት 12 ሆስፒታል መላካቸውን አረጋግጠዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር