በሐዋሳ የሚቋቋመው ኢንዱስትሪ ዞን የውጭ ኩባንያዎችን ትኩረት ስቧል

የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ኢንዱስትሪ ዞን የበርካታ ኩባንያዎችን ትኩረት በመሳቡ፣ በዚህ የኢንዱስትሪ ዞን ኢንቨስት ለማድረግ የቻይና፣ የህንድና የሲሪላንካ ኩባንያዎች ቦታ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ዋና አማካሪና ልዩ ረዳት አቶ አኒሳ መልኮ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእነዚህ ኩባንያዎች ጥያቄ እየታየ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት በቅርብ አራት ከተሞችን የኢንዱስትሪ ቀጣናዎች አድርጎ መርጧል፡፡ እነዚህ ከተሞች አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻና ሐዋሳ ናቸው፡፡ 
በሐዋሳ አንድ ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ሁሉም ነገር የተሟላለት የኢንዱስትሪ ዞን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ በ275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሐዋሳ ከተማ በቅርቡ የአውሮፕላን ማረፊያ እንዲገነባ በመወሰኑ፣ በርካታ ኢንቨስተሮች ትኩረት እንዲያደርጉ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
 አቶ አኒሳ እንዳሉት ከአውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እስከ ሐዋሳ ከተማ ድረስ፣ እንዲሁም ከሐዋሳ አልፎ እስከ ኬንያ ድረስ የባቡር መስመር ይዘረጋል፡፡ የባቡር መስመር የሚዘረጋ ከሆነ በርካታ ኩባንያዎች በሐዋሳ ኢንቨስት ለማድረግ ከወዲሁ ፍላጎታቸውን እንደገለጹም ታውቋል፡፡
በሐዋሳ የሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን በተለይ አግሮ ፕሮሰሲንግ ላይ እንደሚያተኩር አቶ አኒሳ ገልጸው፣ አካባቢው የግብርና ምርቶች በሰፊው የሚገኙበት በመሆኑ የኢንዱስትሪ ዞኑ ጠቀሜታ የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ቀደም ብሎ ለኢንዱስትሪ የተከለለው ቦታ ላይ ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ሞሐ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ፣ ጋትስ አግሮ ኢንዱስትሪና የመሳሰሉት ኩባንያዎች ምግብና መጠጦችን በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ 
ከሐዋሳ በተጨማሪ እየተገነቡ የሚገኙት ኮምቦልቻና ድሬዳዋ እንዲሁ የበርካታ የውጭ ኩባንያዎችን ትኩረት እየሳቡ መሆናቸው እየተገለጸ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ቀጣናዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሰሎሞን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢንዱስትሪ ዞኖቹ የመሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው የሚገነቡ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሐዋሳን ጨምሮ ሁሉም ከተሞች የትራንስፖርት አውታሮች የሚኖራቸው በመሆኑ፣ የገቢና የወጪ ንግድ ለማስፋፋት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር