የጊዳቦ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት 47 ነጥብ 80 በመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ


አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2005(ዋኢማ) - በኦሮሚያና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በመገንባት ላይ ያለው የጊዳቦ የመስኖ ልማት ግድብ ፕሮጀክት 47 ነጥብ 80 በመቶ መጠናቀቁን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በዘንድሮው የበጀት ዓመትም የጊዳቦን የመስኖ ልማት ግድብ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት በ303 ሚሊየን 386 ሺ ብር በ2002 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ግንባታው የተጀመረ መሆኑን ገልፀው፤ በዘንድሮው የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ብዙነህ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ለማጠናቀቅም በዘንድሮው የበጀት አመት 95 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ የቁፋሮ፣ የግድብ አፈር ሙሌት፣ ቁፋሮ፣ የኮንክሪት ስራና የውሃ ማውጫ ግንባታ ቁፋሮና ኮንክሪት ሙሌት ስራዎችን ለማጠናቀቅ ታቅዷል ብለዋል።

ግድቡ 20 ነጥብ 80 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ሲሆን ርዝመቱም 269 ሜትር እንደሚኖረው ጠቁመው፤ ግድቡ ሲጠናቀቅም  117 ነጥብ 82 ሚሊየን ሜትር ኩብ ውሃ የማጠራቀም አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ይህም 7 ሺ 374 ሄክታር መሬትን በመስኖ ሊያለማ የሚችል ሲሆን፤ በዚህም 79 ሺ 820 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል አቶ ብዙነህ ገልፀዋል።

የግንባታ ማሽነሪዎች አቅርቦት አናሳ በመሆኑና የአካባቢው የክረምት ወቅት መርዘምን ተከትሎ በተፈለገው ፍጥነት ለመስራት አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት በሚፈለገው መጠን ፕሮጀክቱ እየሄደ አለመሆኑን ጠቁመው፤  ችግሩን በመፍታት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ብዙነህ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር